የሃይል(የስልጣን) ምንጭ sources of political power

 የሃይል(የስልጣን) ምንጭ (Sources Of Power)

አምባገነን ባለስልጣናት የፖለቲካ ሃይል ወይም ስልጣን በተፈጥሮ ከላይ ወደታች የሚፈስ ቋሚ እና የማይነቃነቅ ተደርጎ እንዲታሰብ ይፈልጋሉ። ሃይል ወይም ስልጣን በብቸኝነት እነሱ ከሚዘውሩት መንግስታዊ ተቋም እንደሚመነጭ ደጋግመው ይነግሩናል፣ ህዝብ ያለ መሪዎቹ አቅም አልባ እንደሆነ ሊያሳምኑን ይጣጣራሉ ሆኖም እውነታው ተቃራኒ ነው፣ አገዛዞች ያለ ህዝብ ትብብር እና ታዛዥነት በራሳቸው መፈፀም የሚችሉት አንዳች ነገር የለም። በአንድ  ማህበረሰብ ውስጥ ብቸኛው የሃይል ወይም የስልጣን ምንጭ ግለሰቦች እና ስብስቦች በተለያየ መንገድ ለድጋፍ ምሰሶዎች ከሚሰጡት ትብብር እና ታዛዥነት የሚገኝ ነው። ምስል ቁጥር 2 እንደሚያሳየው ህዝብ የሁሉም ሃይል ምንጭ በመሆኑ ተቋማት እነዚህን የሃይል ምንጮች እንደ ቧንቧ እየሳቡ ከላይ ለተቀመጡ ባለስልጣናት ያቀርባሉ።

እንደ ዶ/ር ጂን ሻርፕ አገላለጽ የሃይል ወይም የስልጣን ምንጭ ከህዝብ ከሚገኝ ህጋዊነት (የበላይነት)፣ የሰው ሃይል፡ እውቀት እና ችሎታ፣ ቁሳዊ ሃብት፣ የማይዳሰሱ (ስነልቦናዊ) ምክንያቶች እና ማስገደድ  እንደሆኑ ያስረዳሉ።

ምስል ቁጥር 2 ምንጭ USIP የስልጠና ሰነዶች ተወስዶ በከፊል የተለወጠ

  • ህጋዊነት ወይም የበላይነት (Authority)

ስልጣን የተቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎች ብዙሃኑን የማስተዳደር ህጋዊ ስልጣን አላቸው የሚል እምነት መኖር ተከትሎ ከከፍተኛ አመራሮች፣ከባለስልጣናት እና ከተቋማት ወደ ህዝብ  የሚወርዱ ትዕዛዞች በህዝብ መከበር እና መታዘዝን የሚገልጽ ነው። በአቋራጭ የመሪነትን ቦታ የያዙእና ተቃውሞ የበዛባቸው ባለስልጣናት ያገኙትን የበላይነት (ህጋዊነት) ለማቆየት የተጭበረበሩ ምርጫዎችን እንደመሳሪያ ይገለገሉበታል።

  • የሰው ሃይል(Human Resources)

የባለስልጣናትን ትእዛዞች የሚያስፈጽሙ ብዛት ያላቸው ሰዎች መኖር ያመለክታል፣ስልጣን ለማስጠበቅ የሚያስፈልጉ ስራዎችን በተፈለገው ብዛት ጥራት በታዘዙት መሰረት፣ አስፈላጊ የሆነ ክህሎት ተጠቅመው በመደበኛነት የዘወትር ስራቸውን በታዛዥነት የሚሰሩ በርካታ ሰዎች ማግኘትን ይመለከታል። ስልጣን የተቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎችን ማገልገል ትክክል ነው የሚል አመለካከት ህዝብ ላይ በመፍጠር የድጋፍ ምሰሶዎች ያልተገደበ የሰው ሃይል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

  • እውቀትና ክህሎት (Skills and Knowledge)

ስልጣን የተቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎች  በስልጣን እንዲቆዩ የሚረዳ እውቀት እና ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። በዋናነት  ሁሉንም የድጋፍ ምሰሶዎች የሚያንቀሳቅስ እውቀትና ክህሎት ያካበተ የሰው ሃይል በበቂ ቁጥር ማሰባሰብን ይገልጻል። እውቀትና ክህሎት ያካበቱ ተሰሚነት ያላቸው ሊሂቃን ስልጣን ለተቆጣጠሩ ጥቂት ግለሰቦች  ሙሉ ታዛዥነት  ወይም ተባባሪነት ባይኖራቸውም በዝምታቸው እንዲተባበሩዋቸው  ይፈልጋሉ።

  • ቁሳዊ ሃብት (Material Resources)

የአገሪትዋን  አጠቃላይ ገንዘብ እና ንብረት ማለትም ቋሚ፣አላቂ፣ተንቀሳቃሽ፣ የተፈጥሮ ሃብት፣መጓጓዣ፣ የመገናኛ አውታሮች እና መሰረተልማቶችን መቆጣጠር ያመለክታል። ባለስልጣናት የተቆጣጠሩትን ሃብት ትብብር እና ታዛዥነት ለመግዛት፣የተቃወማቸውን ለመቅጣት ይጠቀሙበታል፡፡ በተለይ ያለ ብዙ ወጪ ብዙ ገቢ የሚያስገኝ የከርሰ ምድር ማዕድን ትልቅ የሃይል ምንጭ በመሆን ያገለግላል።

  • የማይዳሰሱ (ስነልቦናዊ) ምክንያቶች (Intangible Factors)

ስልጣን ለተቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎች ተገዢ የሚያደርጉ የስነ-ልቦና እና የባህል ተፅእኖዎችን  ይወክላል። ለባለስልጣናት ትብብር እና ታዛዥነት በሚያስገኝ መልኩ ተዛብተው የተቀረፁ ማህበረሰባዊ ልምዶች፣ አመለካከቶች፣ባህሎች፣ወጎች፣ሃይማኖታዊ እሴቶች፣ርዕዮት ዓለማዊ ሃሳቦች፣ስነ-ልቦናዊ ውቅሮችን ይመለከታል። አገራዊ ብሔርተኞች ነን የሚሉ ባለስልጣናት ራሳቸውን አገር አድርገው በማቅረብ አይነኬ ማንነት ይገነባሉ።

  • ማስገደድ (Sanctions)

ከባለስልጣናቶች ትእዛዝ የሚያፈነግጡ ሰዎችን የመቅጣት አቅም ችሎታ እና መብት ያመለክታል። የአስገዳጅነት ዋና ግብ ከባለስልጣናት የሚወርዱ ትእዛዞችን በማያከብሩ ወይም ጭቆናን በሚቃወሙ ዜጎች ላይ የሚወሰዱ ቅጣቶችን ማህበረሰብ ተመልክቶ ከተከለከሉ ተግባራት ራሱን እንዲያቅብ የሚያደርግ ፍርሃት መፍጠር ነው። በዋናነት ማስገደድ ታዛዥነት የሚፈጥር ፍርሃት ማስፈን እንጂ የተቃወመን ሁሉ መቅጣት አይችልም።

ጠቃሚ ነጥብ

የትኛው የድጋፍ ምሰሶ ምን አይነት የስልጣን ምንጭ እንደሚጠቀም ወይም እንደሚያስፈልገው ካወቅን፣ በተዋረድ  የትኛው የድጋፍ ምሰሶ ለባለስልጣናቶች በስልጣን መቆየት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ከለየን፣አንድ የሃይል ወይም የስልጣን ምንጭ ሲቋረጥ አቅም የሚያጡ የድጋፍ ምሰሶዎችን እና በተዋረድ ሃይል የምንነፍጋችውን ባለስልጣናት ግልጽ ያደርግልናል። ይህ መረጃ አገዛዞችን ፊትለፊት ሳንፋለም የፖለቲካ ስልጣናቸውን ከምንጩ ለመበጠስ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን፣ዘመቻዎችን እና ታክቲኮችን የመንደፍ ስራን ያቀላል።