campaigns/ዘመቻ

ከባለስልጣናት ምቾት በፊት የብዙሃንን ረሃብ ማስታገስ ይቅደም! ዘመቻ
Sell the Cars Pay the People.

ለመላው በፍትህ እና በእኩልነት ለምታምኑ ዜጎች የቀረበ የመብት ማስከበር ዘመቻ ጥሪ!! ከባለስልጣናት ምቾት በፊት የብዙሃንን ረሃብ ማስታገስ ይቅደም!

በከተማችን አዲስ አበባም ሆነ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ ከቁጥጥር ውጪ ከወጣ ውሎ አድሯል። ይህንን የኢኮኖሚ ቀውስ ካባባሱት ምክንያቶች መካከል የፖለቲካ ስልጣን ማስጠበቅን ማዕከል ያደረገ መድልዎ እና የባለስልጣናት የጥቅም ትስስር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። በተለይ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ካላቸው መጠን ያለፈ ፍላጎት የተነሳ፣ የበታች አመራሮቻቸውን የተንደላቀቀ ህይወት በማኖር ወንበራቸውን ነቅተው እንዲጠብቁላቸው ያለአግባብ የህዝብን ሃብት ያፈሳሉ። በተቃራኒው ደግሞ ወርሃዊ ወጪያቸውን ለመሸፈን የማያስችል ደሞዝ እየተከፈላቸው የሚለፉት የመንግስት ሰራተኞች ግን፣ የሚበሉት አጥተው እንደ ነዳያን ፌስታል ይዘው በየሆቴሉ ጓሮ ተሰልፈው ትራፊ የሚለምኑበት ጊዜ መሆኑ፣ በባለስልጣናቱ የሚፈፀመውን በደል እጅግ መራር ያደርገዋል።

የዚህ ግፍ አንዱ መገለጫና የዘመቻችን ዋና አጀንዳ የሆነው ጉዳይ፣ በ2017 የበጀት አመት ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል በሚል ሽፋን፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ በስሩ ለሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቁጥራቸው 44 የሚደርሱ ቅንጡ መኪናዎችን በሽልማትነት አበርክቷል። መስተዳድሩ ለባለስልጣናቱ ምቾት በማሰብ  በአጠቃላይ  ከ300ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ቅንጡ መኪኖችን ሲሸልም፣ ስለምስኪኖቹ  የመንግስት ሰራተኞች የኑሮ  ሁኔታ እና ስቃይ ግድ እንደማይሰጠው አረጋግጦልናል።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ የአዲስ አበባን ችግር ተደራራቢነት እና አደገኛነት ይገነዘበዋል ብለን እናምናለን፡፡ የከተማችን ህዝብ የተሸከመውን መከራ መቋቋም አቅቶት ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ቀውስ ውስጥ ከገባን፣ ከተዳከመው የአገራችን ውስጣዊ ደህንነት ጋር ተደምሮ አጠቃላይ ውድቀት እንደሚከሰት ግልጽ ነው፡፡
 
ስለዚህ ይህ ዘመቻ ከተማችንን አዲስ አበባን ብሎም አገራችንን የማትረፍ ትልቅ ግብ አንዱ አካል መሆኑን ተገንዝበው ዘመቻችንን እንዲቀላቀሉ በአክብሮት እየጠየቅን የበኩልዎን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ግብረሃይላችን በታላቅ አክብሮት ጥሪ ያቀርባል።
 
መኪኖቹ ይሸጡ ግብረሃይል።
#መኪናዎቹይሽጡስራተኞችይደጎሙ
#SellTheCarsPayThePeople 
ኢሜል: sellthecars@gmail.com