የግንኙነት ካርታ (Relationship Map)
አምባገነን መሪዎች በስልጣን መሰላል ጫፍ ለመድረስም ሆነ በስልጣን ለመቆየት ሰፊ እና ጠንካራ የግንኙነት መረብ መዘርጋት ያስፈልጋቸዋል። የግንኙነት መረብ ካርታ የምንስለው በስልጣን ጫፍ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ የፈጠሩት ግንኙነት ምን እንደሚመስል በምስላዊ አቀራረብ ስለሚያስረዳን ነው። በካርታችን ውስጥ ነጥብ ወይም (Nodes) በሚል ስያሜ የምናሰፍራቸው ማንኛውም ከአምባገነን መሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የድጋፍ ምሰሶዎች እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ከፍተኛ ሃይል የተጠራቀመባቸው ነጥቦች (Pressure Points) የት እንዳሉ እና ከማን ጋር እንደሚገናኙ ያሳየናል፡፡ በነጥቦች መሃል የሚሰመሩ መስመሮች የግንኙነት አይነቶችን ያሳውቀናል እንደ ደካማ፣ጠንካራ፣ የላላ ወይም ቅራኔ ውስጥ የገባ ግንኙነት እንዳላቸው ይለይልናል። በአጠቃላይ የግንኙነት መረብ ካርታ በባለስልጣናት እና በነጥቦች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ጥርት አድርጎ ያቀርብልናል።
የግንኙነት መረብ ካርታ መሳል የታክቲክ መረጃዎችንም ያቀርብልናል ለምሳሌ የማወክ እና የማስማማት እርምጃዎች የሚሸነፉ የላሉ ወይም ደካማ ነጥቦችን እና ግንኙነቶችን ለመለየት ያስችለናል።
የተዋጣለት የግንኙነት ካርታ ለመሳል ጠቃሚ ቅደም ተከተል
ካርታው ያስፈለገበት ምክንያት እና ግብ መግለጽ
ለምሳሌ የንቅናቄው አላማዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ነጥቦች (Nodes) ትእዛዝ ከሚሰጧቸው ባለስልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመረዳት የሚሰራ ካርታ ሊሆን ይችላል። ስትራቴጂዎችን እና ታክቲኮችን ለመፈተሽ ወይም አጠቃላይ የአምባገነን መሪዎችን ግንኙነት ለማጥናት የሚሰራ ካርታ ሊሆንም ይችላል።
የነጥቦች (Nodes) አይነት ዝርዝር
ከባለስልጣናት ጋር የቅራኔም ሆነ የትብብር ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችሉ ማንኛውም ነጥቦች ዝርዝር።
ለምሳሌ
ባለስልጣናት:- የክልል፣ፕሬዘዳንቶች፣ሚኒስቴሮች፣ጠቅላይ ሚኒስትር፣ጄነራሎች ወዘተ…
የድጋፍ ምሰሶዎች:- ፖሊስ፣ሜዲያ፣ነጋዴ፣ሲቪል ሰርቪስ ወዘተ…
ንቅናቄው እና አጋሮቹ:- አገዛዙን የሚቃወሙ ሃይሎች፣ህዝብ፣ህዝባዊ አደረጃጀቶች፣ንቅናቄው ወዘተ…
ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች:- ጋዜጠኞች፣ታዋቂ ሰዎች ወዘተ…
ሃሳባቸውን ሊቀይሩ የሚችሉ:- የዳር ተመልካች ምሁራን፣ከአገዛዙ የግንኙነት መረብ በርቀት ያሉ ተቋማት፣መካከለኛው የቢሮክራሲ ክፍል ወዘተ…
አጋር መንግስታት:- ማንኛውንም ድጋፍ የሚሰጡ ጎረቤት አገራትም ሆኑ ሃያላን አገራት።
ነጥቦችን ማገናኘት
ነጥቦችን በመስመሮች የምናገናኘው ንቅናቄው የቆመለትን አላማ ለማፈን፣ስልጣን ለማራዘም ወይም ጭቆናን ለማስቀጠል የተፈጠሩ ግንኙነቶችን የሚወክሉ መስመሮች ናቸው። ማን ከማን ጋር እንደሚገናኝ፣የእዝ ሰንሰለት ውስጥ ማን ማንን እንደሚያዝ እና ከፍተኛ ስልጣን የት እንዳለ ለማየት ያስችለናል። አንዳንድ ነጥቦች እና ግንኙነቶች በግልፅ የሚታወቁ ላይሆኑ ይችላሉ ስለዚህ በድብቅ ወይም ኢመደበኛ ግንኙነቶችንም መፈተሽ ያስፈልጋል።
የግንኙነት መስመር አይነቶች እና ማብራሪያ
ነጥቦችን ባልተቆራረጠ ወፍራም መስመር ስናገናኛቸው ቀጥተኛ እና ጠንካራ የምንለው በፍርሃት፣በግል ትውውቅ፣በቤተሰብ፣በርእዮት አለም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል። በተቆራረጠ መስመር ስናገናኛቸው የላላ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል። ቀጠን ባሉ መስመሮች የሚገናኙ ነጥቦች ደካማ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል ግንኙነቱን የሚያቆይ ጥቅም ትስስር እስካልተቋረጠ ወይም ዘላቂነቱ አስጊ እስከሚሆን ግንኙነቱ ላይቋረጥ ይችላል። በመስመሮቹ ጫፍ የሚኖረው ቀስት ማን ተጽእኖ እንደሚያሳድርባቸው ወይም የበላይነት ያላቸው ነጥቦችን ያመለክታል። በዚግዛግ መስመሮች የተገናኙ ነጥቦች ቅራኔ እንዳላቸው ያሳያል። በነጥቦች መካከል የተሰመረ መስመር በመካከል የተበጠሰ ከሆነ ነጥቦቹ ያላቸው ግንኙነት የተቋረጠ መሆኑን ያመለክታል።
ቀጥተኛ ግንኙነት:- ቀጥተኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸውን ነጥቦች ቀስቶች በሁለቱም ጫፎች አሉ።
ጠንካራ ግንኙነት:- ወፈር ባለ መስመር የሚገናኙ ነጥቦች ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል።
በተዘዋዋሪ የሚገናኙ:- ምንም አይነት የሚያገናኝ መስመር በመሃላቸው ያልተሰመረ ነጥቦች።
ደካማ ግንኙነት:- ጥቅማጥቅም፣ደህንነት (በሰጥቶ መቀበል) ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ቀጠን ባለ መስመር ይወከላል —
የላላ ግንኙነት:- በማህበረሰባዊ ጫናዎች፣በሜዲያ ግፊቶች፣ከብዙሃን ላለመነጠል ግንኙነት የፈጠሩ በትቆራረጠ መስመር ይወከላል – – –
ቅራኔ ውስጥ የገቡ ግንኙነቶች:- የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ንቅናቄው፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የቀድሞ ባለስልጣናት ወዘተ
የተቋረጠ ግንኙነት:-በመካከሉ የተበጠሰ መስመር የነጥቦቹ ግንኙነት እንደተቋረጠ ያመለክታል —/ /—
የነጥቦች አይነት
ሃይል የተጠራቀመባቸው ነጥቦች (Power Center):- የምንለው በርካታ ግንኙነት ያለው ነጥብ ሲሆን በርካታ ወፍራም መስመሮች እና ቀስቶች ወደ ውጭ የሚያመለክቱበት ነጥቦችን ነው።
አገናኝ ነጥቦች:- በቁጥር በርካታ ነጥቦችን የሚያገናኝ ነጥብ።
በርቀት ያለ ነጥብ: ጥቂት ግንኙነት ያላቸው ነጥቦች ሲሆኑ ሊከዳ የሚችል ነጥብ ነው።
ቁልፍ ነጥብ (Pressure Point):- የነጥብ ቁልፍነት እንደየ አውዱ ቢለያይም ቁልፍ የምንለው ነጥብ በጣም ወሳኝ ከመሆኑ የተነሳ ጥቃት ከደረሰበት ሰንሰለታማ ውጤት የሚያስከትል ነጥብ ነው። ለምሳሌ የበርካታ ነጥቦችን አቋም እና ውሳኔ ማስቀየር የሚችል ነጥብ ወይም በርካታ ሃይል የተጠራቀመባቸው ነጥቦች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሊሆን ይችላል።
ስትራቴጂያዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ካርታውን ለተግባር ማዘጋጀት
አገናኞችን መለየት:- በተለያየ ምክንያት የማይገናኙ ወሳኝ ነጥቦችን የሚያገናኙ ለምሳሌ የቤተሰብ አባል አደራዳሪዎች (ሽማግሌ)፣ አማካሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣የቀድሞ ባለስልጣናት ወዘተ…
በርቀት ያለ ነጥብ መለየት:- በርቀት ያለ ምናልባት ሊከዳ የሚችል ነጥብ።
የላላ ግንኙነት ያላቸው:- ግንኙነቱ ቢቋረት ወይም የሃይል አሰላለፍ ቢቀየር ብዙ የማይገዳቸው ነጥቦች።
ኢላማዎች:- ከስትራቴጂ እና አቅም አንጻር በቀላሉ እጅ የሚሰጡ ነጥቦችን ኢላማ ልናደርግ እንችላለን በአጠቃላይ ወደ ቁልፍ ነጥቦች የሚያደርሱ ነጥቦችን እና ተፈጥሮአዊ አለመግባባቶች ያሉባቸውን ነጥቦች አስሶ በማግኘት ኢላማችን ልናደርጋቸው እንችላለን።
ባዕዳን ነጥቦች
የባእዳን ነጥቦች ግንኙነት:- የውጭ አገር መንግስታት በቅድሚያ ስልጣን ከያዘ ማንኛውም አካል ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል። ሆኖም የግንኙነቱ አይነት፣የሃይል አቅርቦት አይነት እና የግንኙነቱን ጥንካሬ ወይም ደካማነት በመለየት መስመሮችን እናሰምራለን። በተመሳሳይ ከንቅናቄው እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የፈጠሩትን ግንኙነት በመፈተሽ በተስማሚ መስመሮች ማገናኘት ይኖርብናል።
ባእዳን ነጥቦች ዝርዝር:- ገንዘብ ለጋሽ፣ የዲፕሎማሲ ጫና ፈጣሪ ሃያላን መንግስታት፣ ተሰሚነት ያላቸው አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐን፣ የኢኮኖሚ ግንኙነት የፈጠሩ ኩባንያዎች፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ህክምና፣ ጤና እና ስደተኞች ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች፣ ቅጥረኛ የደህንነት እና ወታደራዊ ድጋፍ ሰጪ ኩባንያዎች።

ምስል ቁጥር 3
የግንኙነት መረብ ካርታ እድሳት
የሁኔታዎችን መለዋወጥ ተከትሎ በየግዜው ካርታችን መታደስ ይኖርበታል። ስልጣን የተቆጣጠሩ አምባገነን ግለሰቦች እና ቡድኖች በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡ ታሳቢ በማድረግ ጠንካራ የነበሩ አጋርነቶች ሊርቁ ይችላሉ። ስለዚህ የሚከዱ፣የሚገዙ፣የሚታፈኑ፣ገዳይ ቡድን የሚላክባቸው ነጥቦች ስለሚኖሩ በየግዜው ያሉበትን አሁናዊ አቋም መከለስ ይኖርብናል።
ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች
- የህዝብን አስተያየት የሚቀርጹ ነጥቦችን መቅረብ።
- የዳር ተመልካች ነጥቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር።
- ገለልተኛ ባይሆኑም ሃሳባችን ሊገዛቸው የሚችሉ ነጥቦችን መቅረብ (ማግባባት)።
- ቁልፍ ነጥቦች የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ የሃይል ምንጮች ማቋረጥ (ማስራብ)።
- በባለስልጣናት እና በነጥቦች መካከል የሰነበቱ ወይም አዲስ አለመግባባቶችን ማስፋት (ልዩነቶችን መጠቀም)።
- በንቅናቄው እና በባለስልጣናት የጋራ ተፅእኖ ስር ያሉ ነጥቦችን መጠቀም።