የስልጣን (የሃይል) ግንኙነት political power relationship

የስልጣን (የሃይል) ግንኙነት (Power Relationship)

በስልጣን ጫፍ ላይ የተቀመጡ አምባገነን ግለሰቦች የተቆጣጠሩትን የመሪነት ቦታ ይዘው እንዲቆዮ የሚያስችል ሃይል የሚያገኙት በተፈጥሮ ካላቸው ​​ውስጣዊ ሃይል ወይም ተሰእጦ ሳይሆን ከቡድኖች፣ከግለሰቦች፣ከድጋፍ ምሰሶዎች ጋር በሚፈጥሩት ግንኙነቶች ነው።  እነዚህ ግንኙነቶች ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ  እና ማህበራዊ  ድጋፎችን እንዲያቀርቡ የተዘረጉ በአየር ማስተላለፊያ ቧንቧ የሚመሰሉ የግንኙነት መስመሮች ናቸው።

የአንባገነን መሪዎችን ስልጣን ከመአከሉ ለማዳከም ወይም መሪዎችን ከስልጣናቸው ለማስወገድ ስናቅድ የግንኙነት መስመሮችን በዝርዝር መረዳት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፣ ምክንያቱም  ስልጣን ለመንጠቅ የሚደረጉ እርምጃዎች ውጤታማ የሚሆኑት ወሳኝ የግንኙነት መስመሮችን ነጥለን ማቋረጥ ስንችል ብቻ ነው።  ብዙ የተለፋባቸው የለውጥ ሙከራዎች አንባገነን መሪዎች ላይ ተፈላጊውን ጫና ማሳደር የማይችሉት በሃይል ግንኙነት ላይ ጉልህ ሚና በሌላቸው ምናልባትም አንባገነን መሪዎች ሆን ብለው  ያቀናበሩት ኢላማዎች ላይ በማነጣጠር ጉልበታቸውን ስለሚያባክኑ ነው።

የሃይል ግንኙነት አይነቶች

የጥገኛ ግንኙነት:- ባለስልጣናት የተቆጣጠሩትን ከፍተኛ ስልጣን ለማስጠበቅ በፖሊስ፣በጦር ሠራዊት፣በሲቪል ሰርቪስ፣በሚዲያ ወዘተ… ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ይወክላል። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ  በሚኒስቴር  መስሪያ ቤቶች ላይ ያለው የጥገኛ ግኙነት ያመለክታል ።

ያልተመጣጠነ ግንኙነት:-  አንዱ ወገን በሌላው ላይ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው።

ለምሳሌ ባለስልጣናት  በፍትህ አካላት ላይ ያላቸው የበላይነት፣ፖሊስ  እና የጸጥታ አካላት በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያላቸው የበላይነት፣ከፍተኛ ባለስልጣናት ፓርላማ አባላት ላይ ያላቸው የበላይነት ወዘተ.. ግንኙነቶችን ያመለክታል።

ከግንኙነት ነፃ:- በየትኛውም የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ በተናጠል መቆም የሚችል  ሃይል የለም፣አንዳንዶች ራሳቸውን የቻሉ ቢመስሉም በመሰረታዊ አገልግሎት፣በህግ፣በፖሊሲ፣በሙስና ወይም በጸጥታ ሃይል ተፅእኖ እና  ቁጥጥር ስር ናቸው።

ተመጋጋቢ ግንኙነት:- አምባገነን መሪዎች በሚቆጣጠሩት አገር ውስጥ ተመጋጋቢ የሃይል ግንኙነቶች  አይኖሩም ብዙውን ግዜ ተመጋጋቢ ግንኙነት የሚፈጠረው  ተመጣጣኝ ወይም ተቀራራቢ አቅም እና ፍላጎት ያላቸው መሃል ነው። የአምባገነኖች ተፈጥሯዊ ባህሪ የተነሳ ከነሱ እኩል ወይም ተቀራራቢ ሃይል እንዲፈጠር አይፈቅዱም፣የበታች መዋቅሮች እንኳን ያለነሱ እውቅና እና ቁጥጥር ተመጋጋቢ ግንኙነቶችን እንዳይፈጠሩ ከፍተኛ ክትትል ያደርጋሉ። 

የሃይል ግንኙነት የሚፈጠርበት ምክንያቶች

በሃይል የተገደዱ ሰዎች:- በተለያዩ ማስፈራራቶች እና ቅጣቶች ተገደው ከባለስልጣናት ጋር የሃይል ግንኙነት የፈጠሩ ሰዎችን ያመለክታል። ለምሳሌ መካከለኛ እና ከፍተኛ እርከን ላይ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ተሰሚነት ያላቸው ወይም ታዋቂ ሰዎች፣የተለየ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ሰዎች ግንኙነት የሚፈጥሩት ባለስልጣናቱን ስለሚደግፉ ሳይሆን እምቢ ማለት የሚያስከትለውን እስር እና ሌሎች ቅጣቶችን በመፍራት ነው።

የግል ፍላጎትን ለማሟላት:- ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ዝና፣ተፅእኖ፣ክብር ወዘተ… የሚፈልጉ ሰዎች ከባለስልጣናት ጋር የሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች ናቸው። ለምሳሌ ነጋዴዎች ወይም ኢንቨስተሮች የገበያ ቁጥጥር፣የመንግስት ፕሮጀክቶች ወይም ከቀረጥ ነፃ ለማግኘት በፈቃደኘነት የሃይል ግንኙነት ይፈጥራሉ።

ራስን ለማዳን:- በባለስልጣናቶች ተግባራት ባይስማሙም ለመኖር ሲባል የሚፈጠር የሃይል ግንኙነት ነው። ለምሳሌ ባለሃብቶች፣ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች፣መሰረተ ልማት ግንባታ እና አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሰዎች፣እዳ እና ብድር ያለባቸው በርካታ ሰራተኛ የሚያስተዳድሩ ባለሃብቶች ንብረታቸውን ላለማጣት የሚፈጥሩት የሃይል ግንኙነት ነው።

በተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ:- የስራ ድርሻቸው የሆኑ ሰዎች አለቆችን በመታዘዝ የሚፈጠር የሃይል ግንኙነት ይወክላል። ለምሳሌ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እንደ ፖሊስ፣መከላከያ፣ ፍርድ ቤት፣ ባንክ ወዘተ… የሚሰሩ ሰዎች ኢፍትሃዊ ትእዛዞችን የሚያከብሩት በስራ ገበታቸው ላይ ለመቆየት፣ ቤተሰብ ለማስተዳደር ከማሰብ የሚፈጠር የሃይል ግንኙነት ነው።

የሚስማሙ:- በባለስልጣናቶች አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና በጥልቅ የሚያምኑ ሰዎች።

ለምሳሌ በባለስልጣናቶቹ ንግግር ተማርከው ግንኙነት የፈጠሩ፣በሜዲያ ፕሮፖጋንዳ የተጠለፉ ሰዎች፣ለፓርቲው አመለካከት ራሳቸውን የሰጡ ታማኝ ሰዎች፣በትርክቶች እና በአስተምህሮቶች የተቀረጹ ሰዎች፣በሃይማኖት እና በአካባቢያዊ ማንነት የሚቀራረቡ ሰዎች፣ጨቋኝም ቢሆን አገር መሪ ያስፈልጋታል የሚል እምነትያላቸው ሰዎች።

ዋና ነጥብ

አምባገነን ባለስልጣናቶች ከድጋፍ ምሰሶዎች ጋር ያላቸው የጥገኝነት ግንኙነት ያልተረጋጋ እና በማንኛውም ግዜ ሊከዳቸው የሚችል ነው  ምክንያቱም አምነውበት፣ፈልገው እና ተደስተው የግንኙነት መስተጋብር ውስጥ የሚቆዩ ሰዎች በቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ግንኙነቱ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ እና ያልተመጣጠነ በመሆኑም ነው። የድጋፍ ምሰሶዎችም በተመሳሳይ መልኩ  በህዝብ ላይ ጥገኞች በመሆናቸው  የህዝብ ድጋፍ እና ትብብር በማንኛውም ግዜ  ሊከዳቸው ይችላል። በአጠቃላይ አምባገነን መሪዎች የያዙትን ስልጣን የሚያስጠብቁበትን የሃይል ግንኙነት አይነት እና የሃይል ግንኙነት ምክንያቶች ከተረዳን የሃይል አሰላለፍ ለውጥ እንዴት ማምጣት እንደሚቻል ግልፅ ይሆንልናል።

የተመረጡ እና በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሃይል ምንጮች በንቅናቄዎች ጣልቃ ገብነት ወይም ማእቀብ ሲቋረጡ አምባገነን መሪዎች የፈጠሩት አፋኝ የሃይል ግንኙነት ላይ  ሰንሰለታማ ቀውስ ይፈጥራል፣የተቋረጠው የሃይል ምንጭ እንዲቀጥል አምባገነኖች ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ሆኖም ይህንን ፍልሚያ በአሸናፊነት  የሚያጠናቅቀው ጥሩ እቅድ፣ አንድነት እና ስነምግባር የተላበሰ ወገን ነው ።

.

.

.

.

.