የድጋፍ ምሰሶዎች (Pillars of Support)
አምባገነን አገዛዞች በስልጣን ለመቆየት የሚያስፈልጋቸውን ሃብት፣ ህጋዊነት፣ እውቀት የመሳሰሉ ግበአቶችን የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ድርጅት ወይም ተቋም የድጋፍ ምሰሶዎች ብለን እንጠራቸዋለን።
እነዚህ የድጋፍ ምሰሶዎች በህዝብ እና በከፍተኛ ባለስልጣናት መሃል በቆሙ መሰሶዎች ሊመሰሉ ይችላሉ ሆኖም ተግባራቸው በጣም የተገደበ ነው፣ ከከፍተኛ ባለስልጣናት የሚተላለፉ ትእዛዞችን ተቀብለው ወደ ህዝብ በማውረድ ባለስልጣናቱ የሚፈልጉትን ግብአቶች ያቀርባሉ፣ እነዚህ ለባለስልጣናት የሚታዘዙ የድጋፍ ምሰሶዎች አገዛዙ በህይወት የመቆየት ምክንያቶች ናቸው።
እያንዳንዱ ምሰሶ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተዋቀረ ነው፣ በምሳሌነት የቀረበው ምስል ቁጥር 1 ላይ በክብ የተገለጹ በተቋማት ውስጥ ከከፍተኛ ስልጣን እስከ ብዙሃኑ ህዝብ ያላቸውን የሃይል አሰላለፍ ያሳያል። ማዕከል ላይ ጠቆር ብሎ የተቀመጠው በጣም ተፅዕኖ ያላቸው ወይም ባለስልጣናትን የወክላል እንደ ጄኔራሎች፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ፕሬዘዳንቶች ያላቸውን መአከላዊ ስልጣን ያሳያል፣በመቀጠል እየሰፉ የሚሄዱ ክቦች የባለስልጣናቱን የበላይነት በሚያስጠብቅ መልኩ ተዋቅረው እስከ ተራ ዜጎች ያላቸውን የፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ ያመለክታል።
” Pillars of support are institutions and sections of the society that supply the existing regime with sources of power required for maintenance and expansion of its power capacity.”
Dr. Gene Sharp in Waging Nonviolent Struggle”

- ፖሊስ
ሁሉንም የስልጣን ምንጮች በማቅረብ ለአንድ አገዛዝ ፖሊስ እጅግ አስፈላጊ የድጋፍ ምሰሶ ነው፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የበላይነት አለው። በበቂ ቁጥርና በመላው አገር ተሰማርቶየ ሚገኝ የድጋፍ መሰሶ ነው። እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎችን በስሩ የያዘ ነው። በቁሳቁሶች ረገድ የጦር መሳሪያ፣የምርመራ ኤሌክትሮኒክስ፣ ዲጂታል መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪዎች ያሉት የድጋፍ ምሰሶ ነው። ያለ ችግር የሚያስፈልገውን በጀት ያገኛል። ፖሊስ አስገዳጅ ሃይል እንዲጠቀም የሰለጠነተቋም ነው። ፖሊስ በወንጀል መከላከል እና ተያያዥ ተግባራቶቹ ከማህበረሰብ አመለካከቶች ጋር ቁርኝት አለው፣ ለተግባራቶቹ ይሁንታ ወይም ስነልቦናዊ ምክንያቶች ይሰጠዋል።
- የጦር ሃይል (Military)
ፖሊስ እና ጦር ሃይል ተመሳሳይ የድጋፍ ምሰሶዎች ቢሆኑም በአገዛዞች አይን እኩል ላይታዩ ይችላሉ። አንዱ የሚወደድና ጠጋ ጠጋ የሚደረግ፣ ሌላው ደግሞ በአንጻራዊነት ገሸሽ የሚደረግ ሊሆን ይችላል። በሁለቱ ተቋማት መካከልት ኩረት የሚስብ ስንጥቅ ሊኖር ስለሚችል፣ንቅናቄዎች እነዚህን ክፍተቶች በአግባቡ መረዳት ይጠቅማቸዋል።
- የመንግስት ሰራተኞች (Civil Servants)
የመንግስት ሰራተኛ ሁሉንም የሃይል ምንጭ ያቀፈ ነው። አገርን የማስተዳደር እውቀትና ክህሎት አለው። የመንግስት ቁሳቁሶችን እና ንብረቶችን ያስተዳድራል። ህጋዊነት እና የበላይነት አለው። ስለዚህ ሁሉም የሃይል ምንጮች ተጠቃለው በመንግስት ሰራተኞች እጅ ይገኛሉ።
- የትምህርት ተቋማት (Educational System)
መምህራን የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን አእምሮ በእውቀት ያንጻሉ፣ ተማሪዎች ስለራሳቸው ስለአካባቢያቸው እና ስለአገራቸው በሰላ አእምሮ እንዲያስቡ ያግዟቸዋል፣ አገዛዙ ባዘጋጃቸው አስተምህሮቶች መሰረት ህጻናትን እና ወጣቶችን በመቅረጽ የትምህርት ተቋማት አገዛዙን የሚያስቀጥል የሰው ሃይል እና እውቀት ያቀርባሉ። ታዛዥ የሆነ ዜጋ በመፍጠር ጠያቂ አመለካከቶችን በማምከን የበላይነትን ያስፋፋሉ።
- የተደራጁ የእምነት ተቋማት (Organized Religion)
የተደራጁ የእምነት ተቋማት በመላው ምዕመን አስተማማኝ ቅቡልነት እና የማዘዝ ስልጣን አላቸው፡፡ ካህናት፣ ሼኮች፣ ሰበካ ጉባኤና ሌሎችንም ጨምሮ በአገዛዙ ተጽእኖ ስር ከወደቁ የሰው ሃይል፣ እውቀት፣ ቅቡልነት፣ ቁሳቁስ፣ ቦታ የሚያቀርቡ የድጋፍ ምሰሶ በመሆን አገዛዙን ሊያገለግሉ ይችላሉ።
- ሚዲያ(Media)
ሚዲያ የህዝብን ግንዛቤ በመቅረጽ ቁልፍ ሚና አለው። የአገዛዙን ህጋዊነት እና የበላይነት ማረጋገጥ ዋና ተግባሩ ነው። በተጨማሪ የህዝብ አስተያየት በመቀየር የሰው ሃይል በማሰባሰብ፣ አማራጭ አመለካከቶችን በመገደብ፣ እውቀትን እና ልምድ ያላቸው ሰዎች ወደ አገዛዙ እንዲያዘነብሉ በማድረግ፣በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ወይም ወገንተኛ የንግድ ድርጅቶችን በማስተዋወቅ እና በማበረታታት፣አገራዊ ብሄርተኘነትን በማስተጋባት፣ ተቃዋሚዎችን በጠላትነት በመፈረጅ፣ በአገዛዙ ትእዛዝ የሚወሰዱ የሃይል እርምጃዎችን ህጋዊ የሚያደርግ የሜዲያ ሽፋን በመስጠት ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል።
- የንግድ ማህበረሰብ(Business Community)
የንግድ ማህበረሰብ ዋነኛ ዓላማ ትርፍ ማካበት ነው ስለዚህ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ በየትኛውም ስርዓት የንግድ ስራቸው ሳይስተጓጎል እንዴት በትርፋማነታችን እንቀጥላለን የሚል ነው፡፡ በንግድ ማህበረሰብ አማካይኝነት ሰፊው ህዝብ ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ ክህሎቱን ለአገዛዙ እንዲያቀርብ ያደርጋሉ እንደ አስፈላጊነቱም ሃብት እና ቁሳቁስ በቀጥታ ይለግሳሉ።