አዋጪው የትግል ስልት፣ የትጥቅ ትግል ወይስ ሰላማዊ ትግል?   

success rate of armed struggle against civil resistance in Ethiopian analysis.

ጭቆና በቃን፣ ለውጥ ያስፈልገናል ያሉ ሰዎች የሚያልሙትን ነፃ እና ፍትሃዊ ስርአት ለመፍጠር በዋናነት ሁለት የትግል አማራጮች ይጠብቃቸዋል፣ የትጥቅ ትግል ወይም ሰላማዊ ትግል። ከነዚህ ሁለት የለውጥ አውራጎዳናዎች አንዱን ለመምረጥ የሚረዳ መረጃ ወይም ትንተና ባለመኖሩ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ምርጫ በስሜት የተነሳሳ አልያም በአንዱ የትግል ራእይ እና መሪ ተማርኮ ከመወሰን በዘለለ ህይወታችንን፣ ግዜያችንን እና ሃብታችንን ለምንሰጥለት ትግል አዋጪነት ጠለቅ ያለ መረዳት የለንም። ስለዚህ ለውጥ ያስፈልገናል የምንል ኢትዮጵያዊያን ወደ ትግል ፈጥነን ከመግባታቸን በፊት የቀረቡ የትግል አቅጣጫዎችን ተጠቅመው ሌሎች ምን አሳክተዋል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማፈላለግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። 

ይህ ጽሑፍ የበርካቶች ጥያቄ የሆነው የትጥቅ ትግል ያዋጣል ወይስ ሰላማዊ ትግል ለሚለው መልስ ለማግኘት ተጨባጭ የቁጥር መረጃ የሚያቀርብልንን (NAVCO) Nonviolent and Violent Campaigns and Outcome የተሰኘውን የጥናት ውጤት በመንተራስ የትኛው የትግል አቅጣጫ አዋጪ እንደሆነ ለማወዳደር ይሞክራል።

በኢትዮጵያዊያን ስነልቦና ውስጥ የትጥቅ ትግል አዋጪ ነው ተብሎ  በሰፊው ይታመናል፣ ይህም አረዳድ የሚመነጨው ነፍጥ አንስተው ባእዳን ወራሪዎችንም ሆነ ድንበር ዘለል የጎረቤት አገራትን ጦር ድል ያደረጉ አርበኞችን ታሪክ በመዘርዘር የትጥቅ ትግል  አዋጪ ነው የሚል ሰፊ ስምምነት አለ። በቅርብ አመታት የተካሄዱ የእርስ በእርስ ጦርነቶችም ቢሆኑ የትጥቅ ትግል ያዋጣል የሚሉ ክርክሮችን የሚደግፉ ይመስላል፣ የትጥቅ ትግል ውጤታማ ነው አደለም የሚለውን ለማስረዳት የ(NAVCO) ጥናት  በሶስት መሰረታዊ ክፍሎች ይመድባቸዋል።

  1. ጸረ ወራሪ ትጥቅ ትግል (anti-occupation arm resistance)

ድንበር ዘለል የውጭ ወራሪዎች ፍላጎት በዋናነት ጥቅም ወይም ግዛት ማስፋፋት ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ጥቅማቸውን ለመከላከል ሲሉ የሃገር ውስጥ ሃይሎች ውስጣዊ ልዩነታቸውን በመተው በጋራ ይቆማሉ። ይህ ሁኔታ የሰው ሃይል፣ ሃብት፣ እውቀት የመሳሰሉ ወሳኝ ግበአቶች በአገራዊ ስሜት (በሰንደቅ አላማ ዙርያ) እንዲሰባሰብ ምክንያት ስለሚሆን ጸረ ወረራ ትግሎችን የማሸነፍ እድል ከፍ ያደርገዋል።  በተለይ ወራሪው ሃይል በጦርነቱ የሚገጥመውን ኪሳራ ከድል ማግስት ከሚዝቀው ትርፍ ጋር አስልቶ ስለሚመጣ የአክሳሪነት አዝማሚያ ያላቸው ጦርነቶችን እስከ መጨረሻው ደም ጠብታ ለማስቀጠል የሚያስገድድ የሞራል ወይም ራስን የማዳን ጥያቄዎች ስለማይኖርበት ወረራውን በአጭሩ ሊገታ ይችላል። 

ይህንን ሃሳብ በመረጃ አስደግፎ የሚያቀርብልን በሃርቨርድ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው NAVCO የተሰኘ ጥናት ነው። ይህ ጥናት በመላው አለም  ከ1900 እስከ 2006 እ.ኤ.አ የተካሄዱ 323 የትጥቅ እና ሰላማዊ ትግሎችን በጥልቀት ፈትሾ ያወጣው NAVCO 1.1 የተሰኘ የመጀመሪያ እትም እንደሚያስረዳው፣ በተጠቀሰው መቶ አመት ውስጥ የተካሄዱ ጸረ ወራሪ ትጥቅ ትግሎች ማሸነፍ የቻሉት 36% እንደነበረ ያመለክታል፣ በተመሳሳይ ወራሪዎችን ለማባረር ሰላማዊ ትግልን የመረጡ 35% ድል እንደቀናቸው ያሳያል። 

በአጠቃላይ ሁለቱም የትግል አማራጮች ወራሪ ሃይልን በመመከት ረገድ ተቀራራቢ እድል አላቸው የሚል ድምዳሜ ይሰጠናል።  

  1. ፀረአገዛዝ ትጥቅ ትግል (anti-regime arm resistance

በከፍተኛ የስልጣን ጫፍ ላይ የተቀመጡ አፋኝ መሪዎች ስልጣናቸውን ለማጽናት የጦር እና ደህንነት ተቋማትን ትእዛዝ ተቀባይ አድርገው በማደራጀት ወንበራቸውን በወታደር ያጥራሉ፣ በተጨማሪ ራሳቸውን ብቸኛ የአገር አንድነት ዋስትና አድርገው በመሳል ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎች “አገር አፍራሽ ሃይሎች ናቸው” በሚሉ ክሶች የህዝብን አስተሳሰብ ይበርዛሉ፣ የአፈና ማሽኑ ያለበትን የገንዘብ ፍላጎት ለማሟላት መንግስታዊ ተቋማትን ተጠቅመው ከፍተኛ ግብር እና ቀረጥ በማስከፈል ሰፊው ህዝብ በተዘዋዋሪ አምባገነን መሪዎችን  እንዲተባበሩ ያስገድዳሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ለአምባገነን መሪዎች ከፍተኛ አቅም በመፍጠር የፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሉን ውጤታማነት ያሳንሰዋል።  

የ NAVCO 1.1 ጥናት ስለ ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎች ውጤታማነት ሲተነትን ከ1900 እስከ 2006 እ.ኤ.አ የተካሄዱ ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎች  የአጭር ግዜ ግባቸውን (ጨቋኝ ቡድን ወይም አገዛዝ ከስልጣን ማስወገድ) የቻሉት 23% ብቻ እንደነበሩ ያሳያል፣ በሌላ ጎን ሰላማዊ ትግልን ተጠቅመው አገዛዞችን ለማስወገድ ከተነሱት ውስጥ 53% ስኬታማ እንደነበሩ ያመለክታል።    

ከላይ በተጠቀሰው ግዜ ገደብ ውስጥ ድል የቀናቸው ፀረ አገዛዝ የትጥቅ ትግሎች ድል ካስመዘገቡበት ግዜ አንስቶ በቀጣይ 5 አመታት ውስጥ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ያሰፈኑት 6% ብቻ ናቸው፣ ቀሪዎቹ ጦርነት ወይም የከፋ አፋኝ አገዛዝ እንደፈጠሩ ጥናቱ ያሳያል። በአንጻሩ በተመሳሳይ ግዜ ገደብ ውስጥ ድል ያስመዘገቡ ሰላማዊ ትግሎች ለውጥ ካስመዘገቡበት ግዜ አንስቶ በቀጣይ 5 አመታት ውስጥ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የፈጠሩት 55% ሲሆኑ  ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመፍጠር ረገድ ከሁሉም የላቀ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል። 

  1. የመገንጠል ጥያቄ ያነገበ ትጥቅ ትግል (secession arm resistance)

ከነበሩበት አገረ መንግስት በመገንጠል የራሳቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችል አዲስ ሉዓላዊ አገር ለመመስረት የሚደረጉ የትጥቅ ትግሎች ለማሸነፍ ከሁሉም የከበደ ግብ እንደሆነ የ NAVCO 1.1  ጥናት ያስረዳል፣ ይህም የሆነው መንግስታት ያላቸውን የቆዳ ስፋት የሚቆርሱ፣ ተጽዕኖ እና ሃብት የሚቀንሱ ጥያቄዎችን ላለመቀበል ሁሉንም አይነት ምድራዊ ጥረት ያደርጋሉ፣ በተመሳሳይ የመገንጠል ጥያቄዎች የአለማቀፍ መንግስታትንም ድጋፍ ለማግኘት ይቸገራሉ። 

የመገንጠል ጥያቄ ያነገቡ የትጥቅ ትግሎችን ስኬታማነት በተመለከተ የNAVCO 1.1 ጥናት ውጤት እንደሚያሳየን ከላይ በተጠቀሰው ግዜ ገደብ ውስጥ ትጥቅ አንስተው አገር መመስረት የቻሉት በአማካኝ 13% ሲሆኑ የመገንጠል ጥያቄዎችን በማስመለስ ረገድ ሰላማዊ ትግል የ10% ውጤት እንደነበረው ያመለክታል። ሆኖም ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲ ከማምጣት አንጻር ስንለካቸው የመገንጠል ጥያቄዎችን በትጥቅ ትግል ካሳኩት መካከል ድል ካስመዘገቡበት ግዜ አንስቶ በቀጣይ 5 አመታት ውስጥ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ያሰፈኑት 0% እንደነበረ በማስቀመጥ ሁሉም ወደ ጦርነት ወይም ወታደራዊ አገዛዝ እንደተሸጋገሩ ጥናቱ ያሳያል። በአንጻሩ በሰላማዊ ትግል አገር መመስረት ከቻሉት ትግሎች ውስጥ 25% የተረጋጋ እና ዴሞክራሲያዊ አገር እንደመሰረቱ ጥናቱ ያስረዳል። 

ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት የትጥቅ ትግል ምድቦች ይዘን የአገራችንን ሁኔታ እንመልከት።

ታሪካችንን መለስ ብለን ስንፈትሽ ከውጭ ወራሪዎች እና በወራሪነት ከተፈረጁ የውስጥ ሃይሎች ጋር የተደረጉ ጦርነቶች በድል እንደተጠናቀቁ ከስር የቀረበው ሰንጠረዥ ያመለክታል፣ ይህም የሆነው በአገራዊ ስሜት የተነሳሳ ህዝብ በአድ ከሚለው ሃይል ጋር በሙሉ ሃይሉ በጋራ በመዋጋቱ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፣ ሆኖም ዴሞክራሲያዊ አገር ከመፍጠር አንጻር ከተመለከትናቸው ስኬታማ አልነበሩም።

ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎችም ቢሆኑ የሚታገሉለት አላማ ፍትሃዊ ቢሆንም እንኳን በአገራዊ ስሜት የተነሳሳ ትልቅ ቁጥር ያለው ሃይል ለማዝመት የሚችሉበት ሁኔታ ጠባብ በመሆኑ የተራዘመ ትግል ውስጥ አልፈው ስልጣን የያዙት አዲስ አፋኝ አገዛዝ ከመፍጠር የዘለለ የረጅም ግዜ አላማቸውን አላሳኩም።

ከሁሉም ረዘም ያለ ግዜ እና ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቀው የመገንጠል ጥያቄ ሲሆን ትግሉ የተነሳበትን ግብ ቢያሳካም ለህዝብ የሚሰራ ዲሞክራሲያዊ አገረ መንግስት ማቋቋም ግን አልቻለም። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተካሄዱ ትጥቅ ትግሎች በሶስቱም ምድቦች ዴሞክራሲያዊ ስርአት አልፈጠሩም።    

የNAVCO ጥናቶች ላይ ተመርኩዘን በሰላማዊ ትግል እና በትጥቅ ትግል  መካከል የሚታይ ሰፊ የውጤት ልዩነት እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ለመረዳት የጋራ የሆኑ መለኪያዎችን ተጠቅመን ለመፈተሽ እንሞክር። 

  1. የተሳታፊ ቁጥር 

የተሳታፊዎች ቁጥር መብዛት በሁሉም የለውጥ ትግሎች ስኬት ላይ ጉልህ  ተጽእኖ አለው።  ሰላማዊ ትግልን የመረጡ ለውጥ አራማጆች አሸናፊ ለመሆን የሚችሉት ከሚንቀሳቀሱበት አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር ውስጥ በአማካኝ 3.5% የሚሆነውን በንቃት ማሳተፍ ከቻሉ ያለጥርጥር አሸናፊ እንደሚሆኑ የNAVCO ጥናት ያስረዳል፣ ጥናቱ ከዳሰሳቸው በርካታ ናሙናዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ከ3.5% ባነሰ የህዝብ ቁጥር አይበገሬ የሚባሉ አምባገነን መሪዎችን ማንበርከክ እንደቻሉ ያስረዳል። 

በተቃራኒው ከጸረ ወራሪ ትጥቅ ትግል ባሻገር ትልቅ ቁጥር ያለው ጦር አደራጅተው ድል ማድረግ የቻሉ የትጥቅ ትግሎች NAVCO ጥናት ውስጥ አልተመዘገቡም።

በአጠቃላይ የትጥቅ ትግልም ሆነ ሰላማዊ ትግል ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎን ካገኙ ጠንካራ ተገዳዳሪ ሆነው የመውጣት እድል አላቸው፣ ይህንን የሚረዱ አምባገነን መሪዎች የአፈና እና የመከፋፈል እርምጃዎችን በመውሰድ ህዝባዊ ተሳትፎን ለመገደብ ይጥራሉ።  ሰላማዊ ትግል የአፈና እና የመከፋፈል እርምጃዎችን ለመቀልበስ የሚያስችሉ በርካታ ዘዴዎች አሉት ሆኖም የትጥቅ ትግል ዘዴዎች ህዝብን ከአፈና እና ከመከፋፈል ጥቃቶች ተከላክሎ ተሳትፎን ለማሳደግ አስቸጋሪ ያደርገዋል፣ ከዛም አልፎ ተርፎ የትግል ስልቱ በራሱ የሚያስቀምጠው የምልመላ መስፈርቶች የተነሳ አሸናፊ ሊያደርጋቸው የሚችል ሰፊ ቁጥር ያለው ተሳታፊ ለማሰባሰብ ይቸገራሉ።   

  1.  የአካል ብቃት ገደብ (physical barriers) 

የትጥቅ ትግልን የሚቀላቀሉ ሰዎች የተለያዩ የአካል ብቃት መለኪያዎችን ማለፍ ይኖርባቸዋል፣ ለምሳሌ ረሃብ፣ጥም፣ረጅም የእግርጉዞ የመሳሰሉ ጫናዎችን መቋቋም የሚችል ሙሉ ጤንነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፣ በተጨማሪ ሽምቅ ተዋጊዎች አስቸጋሪ መልከአምድር ባላቸው አካባቢዎች ስለሚንቀሳቀሱ ጥሩ የአካል ብቃት ያላቸውን ወጣት ወንዶችን በመምረጥ ሰፊውን ህዝብ ለማግለል ይገደዳሉ፣ ይህም ትግሉ በጥቂት ቁጥር እና ባልተመጣጠነ ህዝባዊ ስብጥር እንዲገደብ ያደርገዋል። 

ሰላማዊ ትግል የተለየ የአካል ብቃት መመዘኛ ስለማይጠይቅ ከተለያየ የማህበረሰብ ክፍሎች የመጡ ሰዎችን ያለገደብ በማቀፍ አገራዊ መልክ ያለው ህዝባዊ ስብጥር ለማሰባሰብ ይፈቅዳል ፣ በተለይ እነዚህ በጋራ የሚሰሩ የተለያየ ማህበራዊ መሰረት ያላቸው ግለሰቦች እና ስብስቦች ወደ ትግሉ ይዘውት የሚመጡትን ልዩ ልዩ እውቀት እና ልምድ በማጣመር ከአገዛዙ የላቀ የለውጥ ሃይል ለማደራጀት ያስችላቸዋል። 

  1. መረጃ እና ግንኙነት ገደብ (information and communication barrier) 

ፀረ አገዛዝ የትጥቅ ትግሎች የሚመሽጉባቸው እና የሚንቀሳቀሱባቸው አድራሻዎች ድብቅ ስለሚሆኑ ሙሉ እምነት የማይጣልባቸው ሰዎች ትግሉን መቀላቀል ይቸገራሉ፣ ስለዚህ ትግሉ በሚተዋውቁ፣ በሚተማመኑ እና ከተወሰነ አካባቢ በተሰባሰቡ ሰዎች ተወስኖ ሊቆይ ስለሚችል ሰፊው ህዝብ ትግሉ ስላለበት  ሁኔታ በቂ መረጃ አይኖረውም። በተጨማሪ ለሚወሰዱ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃዎች ሚዛናዊ መረጃ ማግኘት ስለማይቻል የተሻለ ተደራሽነት ያለው ሜዲያ የሚቆጣጠር ወገን እውነታውን በማዛባት ትርክቱን ለራሱ ጥቅም ሊያውለው ይችላል።

በሰላማዊ ትግል የሚካሄዱ ዘመቻዎችም ሆነ የሚወሰዱ እርምጃዎች ህዝብን ለአላስፈላጊ አደጋ የሚዳርጉ ዘዴዎችን አይጠቀሙም፣ በትለይ የትግሉ አንቀሳቃሾች ህዝብን ከተለያዩ ጥቃቶች ለመጠበቅ አስፈላጊ መረጃዎችን ከስር ከስር በተለያየ የግንኙነት መረቦች በኩል ያደርሳሉ፣ ዘመቻዎችም ቢሆኑ የተሳታፊዎችን እና የአካባቢያዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የትግል ስልት ስለሚነድፉ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች የቀረቡ እርምጃዎችን መርምረው በሚመቻቸው ግዜ እና ቦታ ለመሳተፍ የሚያስችሉ ሰፊ አማራጮችን ያቀርባሉ። ሚስጢራዊነትን በተመለከተ ውሳኔ በሚሰጡ ሰዎች ከሚያዙ የቅድመ እርምጃ እቅዶች ባሻገር ሰላማዊ ትግል መረጃዎችን በሰፊው በማዳረስ ስራ ላይ ያተኩራል።

  1. የቁርጠኘነት ገደብ (commitmental barrier) 

የትጥቅ ትግል የማይተካውን የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል መቁረጥን የሚጠይቅ የትግል አቅጣጫ ነው፣  በተጨማሪ በድልም ሆነ በሽንፈት የተመለሱ ሰዎች ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎችን ሲቀላቀሉ ትተውት የሄዱትን የቀድሞ ህይወት እና ቤተሰብ ተመልሶ የማግኘት እድላቸው በጣም አናሳ ነው፣ አንዳንድ ተዋጊዎች በተራዘመ ትግል የተነሳ  ከሚኖሩበት አካባቢያዊ አስተሳሰብ እና ባህል ተቆራርጠው ሊቀሩም ይችላሉ። 

ሚስጥር ከመጠበቅ አንጻር ወደ ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሉ በዘፈቀደ መግባት እና መውጣት አይፈቀድም ስለዚህ ትግሉ የሚጠይቀውን በርካታ አመታት በዱር እና በዋሻ የማሳለፍ ግዴታን መግባት ይጠይቃል። በእነዚህ የቁርጠኝነት ገደቦች የተነሳ ሰዎች ፀረ አገዛዝ የትጥቅ ትግሎችን በገፍ እንዲቀላቀሉ አይጋብዝም። 

በመርህ ደረጃ ሰላማዊ ትግል የደጋፊዎችንም ሆነ የአንቀሳቃሾችን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጡ የትግል ስልቶችን አይጠቀምም፣ እያንዳንዱ የትግል ስልቶች የባላንጣን ግብረመልሶች እየለካ የትግሉን ሙቀት የመጨምመር ስልት (graduale escalation) ስለሚጠቀም ተሳታፊዎች ከፍተኛ ስጋት ሳይገባቸው ከስራቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ በተመቻቸው ወቅት ይመጥነናል የሚሉትን የትግል ስልቶች መርጠው ለመሳተፍ ይችላሉ። ሆኖም ሰላማዊ ትግል ህይወትን ለአደጋ የሚጋርጥ የትግል ስልቶችን አይጠቀምም ማለት ግን አገዛዙ በሚወስደው የሃይል እርምጃ የህይወት፣ የአካል እና ንብረት ጉዳት አይደርስም፣ እስር እና ማስፈራራት አይኖርም ማለት አይደለም፣ ጠንከር ያሉ ፖለቲካዊ ጥያቄ ካነሱ ሰላማዊ ትግሎች ውስጥ 86% ሃይል የቀላቀለ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው NAVCO ጥናት ያስረዳል።

  1. ሞራል ገደብ 

በተፈጥሮ አንድ ሰው የሌላውን ነብስ የማጥፋት ስነልቦናዊ ዝግጁነት አለው ተብሎ አይታመንም፣  ይህንን ለትጥቅ ትግል የማይመች አመለካከት በመፋቅ ምልምል ተዋጊዎች የተላኩበትን ግዳጅ ያለማንገራገር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ረዘም ያለ ግዜ የሚጠይቅ ስልጠና (ኢንዶክትሪኔሽን) መውሰድ አለባቸው፣ አንዳንድ አመራሮች ስልጠናው የሚወስደውን ግዜ  ለማሳጠር እና ጨካኝ ወታደር ለማፍራት የተመረጡ ጥላቻ ተኮር አስተምህሮቶችን በማስረጽ፣ የሚያደፋፍሩ አደንዛዥ እጾችን በመስጠት፣ እርኩስ መንፈስ መጥራት የመሳሰሉ አቋራጭ ዘዴዎችን ይሞክራሉ። እነዚህ አቋራጭ ዘዴዎች  የትግሉን አቅጣጫ ከማሳትም አልፈው ያልተጠበቁ የጦር ወንጀል የመሳሰሉ መዘዞችን ያመጣሉ።  

ሰላማዊ ትግል የሞራል ተጠያቂነትን ስለሚያስቀድም በርካቶች በቀላሉ ይሳቡበታል፣ የሰው ህይወትን ሳይቀጥፍ የማንንም ሃብት ንብረት ሳያውድም፣ ማንንም ሳያስገድድ በሚያደራጀው እና በሚያሰማራው የለውጥ ሃይል ስለሚተማመን ተሳታፊዎች የትግሉ አካል በመሆናቸው የሞራል ጥያቄ አይኖርባቸውም።

ፀረ አገዛዝ የትጥቅ ትግሉ ከላይ ከ 1 እስከ 4 የተጠቀሱትን ገደቦች አልፎ ትልቅ ቁጥር ያለው ምልምል ተዋጊዎችን ቢያሰባስብ እንኳን ከለላ የሚሰጥ ጎረቤት አገር ካላገኙ በቀር ሰልጣኞችን ከአገዛዙ ጥቃት ተከላክለው ለማሰልጠን፣ ለመቀለብ እና ለማስታጠቅ አይችሉም። እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግሎች ዙሪያ ሰፊ ቁጥር የማሰባሰብን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል። ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ነው፣ ሆኖም ረጅም እና መራር የትግል ጉዞ ያሳለፉ የትጥቅ ትግሎች  በአነስተኛ ቁጥር እና ስብጥር ተገድበው ስለኖሩ ተቃራኒ ሃሳቦችን የማስተናገድ ልምድ አይኖራቸውም፣ ይህ ልምምድ ከድል ማግስት ተጽእኖ በመፍጠር ተቃራኒ ህዝባዊ ፍላጎቶችን ለመስማት ፈቃደኝነት ያሳጣቸዋል ብሎም ወደ ኢፍትሃዊ አሰራር የመንሸራተት እድላቸውንም ያሰፋዋል።

  • የለውጥ ዘዴ

በትጥቅ ትግል እና በሰላማዊ ትግል መካከል የውጤት ልዩነት የታየበት ሁለተኛው ምክንያት የሚጠቀሟቸው የለውጥ ዘዴዎች ናቸው። የትጥቅ ትግል ጠላቴ ነው የሚለውን ሃይል እና የጀርባ ደጀን በጠመንጃ አፈሙዝ እየደመሰሰ ወይም አስገድዶ እጅ እያሰጠ ወደ ድል የመጓዝ ስትራቴጂ ላይ የተገደበ የለውጥ ዘዴ ነው። ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግልም እንዲሁ በአምባገነኖች የሚመራውን የጦር ሃይል እና መንግስታዊ ተቋማትን በመደምሰስ ወይም በመማረክ የተነሳበትን አላማ ለማሳካት ይንቀሳቀሳል፣ በአምባገነን መሪዎች የተገነቡ ወታደራዊ እና ሲቪል ተቋማትን አፈራርስው በአዲስ መንግስታዊ ተቋማት የመተካት አላማ ያነገቡ ናቸው፣ ይህ በጅምላ አፈራርሶ በአዲስ የመገንባት እርምጃ ፈቅደውም ሆነ ተገደው የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን ያለ ልዩነት ኢላማ ስለሚያደርግ፣ የሚመጣው ሃይል ከስራዬ ያፈናቅለኛል ወይም ይገድለኛል፣ በሚል ስጋት በርካቶች አገዛዙን ለመተባበር ይገደዳሉ፣ ይህ ሁኔታ አምባገነን መሪዎች ያለፉበትን ድጋፍ እና ውስጣዊ ጥንካሬ ይፈጥርላቸዋል።  አንዳንድ ፀረ አገዛዝ ትጥቅ ትግል መሪዎች የአገዛዙ ወታደሮች ምድባቸውን ጥለው ቢከዱ አልያም እጃቸውን ቢሰጡ በሰባዊነት እንደሚያዙ ጥሪ ከማድረግ ባሻገር አገዛዙ ካስታጠቀው ጦር ጋር ያላቸው ግንኙነት በጠላትነት የሚተያዩ ባላንጣ ጎራዎች ናቸው።  

የሰላማዊ ትግል የለውጥ ዘዴዎች የሚነሱት “የአምባገነን መሪዎች ስልጣን የሚጸናው  የሚታዘዝ እና የሚተባበር በቂ የሰው ሃይል ሲያገኙ ብቻ ነው” ከሚል መረዳት ነው። ስለዚህ ከጥቂት ውሳኔ ሰጪ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሻገር መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ተራ ዜጎችን  በጠላትነት አይመለከትም። እነዚህን ቁልፍ መሪዎች ነጥሎ በስልጣን ለመቆየት የሚያሰፈልጋቸውን ህዝባዊ ድጋፍ እና ትብብር በመንፈግ ከስልጣን የማባረር የለውጥ ዘዴ ይጠቀማል፣ በተለያየ ምክንያት ያለ ሙሉ ፈቃዳቸው ከአንባገነን መሪዎች ጋር ግንኙነት የፈጠሩ ባለድርሻ አካላት እና ግለሰቦችን አግባብቶ የማስከዳት ዘዴን በመጠቀም ወገንተኘነታቸውን ወደ ህዝብ እንዲያዞሩ ያደርጋል።  

በተለይ የአምባገነን መሪዎች ስልጣን ዘብ ከሆኑ ወታደሮች እና የደህነነት ሰራተኞች ጋር ጥሩ አጋርነት በመፍጠር  እኩይ አላማ ከሚያራምዱ አመራሮች የሚሰጣቸውን ትእዛዞች ተከትለው ወገናቸውን እንዲገድሉ እና እንዲያሰቃዩ የታዘዙ የህዝብ አካል እንደሆኑ አሰረድቶ በማስከዳት አገዛዙ ብቻውን እንዲቀር የማድረግ ድርብ ስለት ያለውን ዘዴ ይጠቀማሉ። ይህ ዘዴ አገዛዙን ከድተው ለሚወጡ ሰዎች በሚሰጠው መተማመኛ የተነሳ በጥቂት ህዝባዊ ግፊት በርካቶች አገዛዙን እንዲከዱ አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።  ይህ ማለት ግን የታጠቀ መንግስታዊ ሃይሎች በሙሉ  የህዝብ ወገን ናቸው ለማለት አይቻልም በአጥፊ አስተሳሰብ የታነጹ ገዳይ ቡድኖችን በጥንቃቄ ለይቶ ይመለከታል።         

የዘመናችን ብልጣብልጥ አምባገነን መሪዎች ቴክኖሎጂው ያፈራቸውን የረቀቁ መሳሪያዎች እና መተግበሪያዎች በመጠቀም የቀደሙ የሰላማዊ ትግልም ሆነ ትጥቅ ትግል እንቅስቃሴዎች ድል ያደረጉበትን አቋራጭ መንገዶች በማጥበብ እና ከፋፋይ አጀንዳዎችን በማሰራጨት የጋራ ራእይ ላይ የተመሰረተንሃይል የመፍጠርን ተግባር ከባድ እና ውስብስብ አድርገውታል፣ ይህም ሁኔታ በቅርብ አመታት ብልጣብልጥ አምባገነኖችን ለማስወገድ የተደረጉ ጥረቶችን ውጤት በከፊል ቀንሶታል። 

ሳሊ አብረሃም